Love your Neighbor

ባልንጀራዬ ማነው?

ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የክርስትና ታሪክ ውስጥ “ደጉ ሳምራዊ” በሚል ስያሜ የሚጠራ ዝነኛ ምሳሌያዊ ታሪክ አለ።ምሳሌው የሚገኘው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ከቁጥር 25 እስከ 37 ሲሆን የተናገረውም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንምሳሌ እንዲናገር ምን አነሳሳው? ነገሩ እንዲህ ነው። ከሚከተሉት ብዙ ሕዝብ ውስጥ ሰባ ሰዎችን መረጠና ወደ ተለያዩከተሞች ከእሱ ቀድመው በመሄድ ሕዝቡን እንዲያገለግሉ ላካቸው። እነርሱም ሄደው በውጤቱ ተገርመው ተመለሱ። ጌታምዳግም ሰብስቦ እያስተማራቸው ሳለ ድንገት አንድ ያልተጠበቀ ሰው ከመካከላቸው ተነስቶ ጥያቄ ሰነዘረ። የሰውየውን ማንነትበተመለከተ ወንጌላዊው ሉቃስ “ሕግ አዋቂ” በማለት ይጠራዋል። በዚያን ዘመን በእስራኤል ምድር የነበሩ ሕግ አዋቂዎችከልጅነታቸው አንስቶ የሙሴን ሕግ ጠንቀቅው የተማሩ፣ ሕጉን የሚተነትኑና የሚያብራሩ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅከበሬታና ማዕረግ ያላቸው ፕሮፌሰሮች እንደ ነበሩ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። ስለ ሰውየው የመደብ ጀርባና ስለ ጥያቄዎቹመነሻ የበለጠ የሚነግረን ይህ ሰው የመጣበትን ቡድን ማወቅ ነው። በዘመኑ በእስራኤል ስመ ጥር የሆኑ ሁለት ዋና ዋናቡድኖች ነበሩ። አንደኞቹ ፈሪሳውያን ሌለኞቹ ሰዱቃውያን። ሁሉም ባይባልም አብዛኞቹ ሕግ አዋቂዎች ከፈሪሳውያን ወገንእንደ ነበሩ ይታመናል። ሰዱቃውያን በዋነኝነት የካህናት ወገን ሲሆኑ ትኩረታቸው ፖለቲካ፣ የሕዝብ አስተዳደር እና ሀብትማፍራት ላይ የነበረ ሲሆን ፈሪሳውያን ግን ለሕግ እና ለአይሁድ ሃይማኖት ቀናኢ ነበሩ።

ይህ ሕግ አዋቂ ከማን ወገን እንደ ነበር ጥያቄዎቹ በግልጽ ያሳያሉ። “የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” የሚለውየመጀመሪያ ጥያቄው በትንሳኤ እንደሚያምን ስለሚጠቁም ፈሪሳዊ እንደ ነበር እርግጠኛ ያደርገናል። ሰዱቃውያን በትንሳኤአያምኑም ነበርና።[1] “ባልንጀራዬስ ማነው?” የሚለው ሁለተኛ ጥያቄም እንዲሁ ከየት ወገን እንደ ነበር ያሳያል። ይህንንያለው ራሱን ለማጽደቅ ፈልጎ በመሆኑ “ባልንጀሮቼን እወዳለሁ ስለዚህ ትዕዛዙን ፈጽሜያለሁ” ለማለት እንደ ፈለገ እናያለን።ይህም ከቡድኑ ማንነት ጋር የሚሄድ ነው። “ፈሪሳዊ” የሚለው ቃል በግሪክ “ተገንጣይ ወይም ተነጣይ” የሚል ትርጉም ያዘለሲሆን በዕብራይስጥ የሚጠሩበት “ኼቨሪም” የሚለው ስያሜ “ጓደኛሞች ወይም ጓዶች” የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህፈሪሳውያን ከተራው ማኅበረሰብ የተለዩ፣ ሕግን ያልተማረውን ሌላውን ሕዝብ የሚንቁ፣ ራሳቸውን የተለዩ አድርገውየሚቆጥሩና የብጤዎቻቸውን ስብስብ ብቻ “ባልንጀራሞች ወይም ጓደኛሞች” ብለው ይጠሩ እንደ ነበር ያሳየናል።

ሕግ አዋቂው “የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” በማለት የጠየቀው በቅንነት ለማወቅ ጓጉቶ ሳይሆን ማወቁንለማሳየትና የጌታን አለማወቅ ለመግለጥ ፈልጎ ነበር። ይህንንም ጸሐፊው ሉቃስ ከጥያቄው ባሻገር የሚያስተጋባውን የልቡን ጥመት “ሊፈትነው ተነስቶ” በማለት ይገልጥልናል። ዳሩ በዕውቀት ራስና በጥበብ ጌታ ፊት መቆሙን ሳያውቅ ሊፈትን ተነስቶተፈትኖ ወድቋል። ጌታ የሱስም ጥያቄውን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ በጥያቄ የመለሰበት ምክንያት ይኸው ነበር።
“በሕግየተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ?” ማለቱ “አንተ ሕግን ጠንቅቄ የማውቅ ነኝ! ከእኔ በላይ ዕውቀት ላሳር! የምትልነህ ስለዚህ መልሱን አንተው ንገረኝ።” ማለቱ ነበር።

ሰውየው ልቡ ጠማማ ይሁን እንጂ መልሱ ትክክል ነበር። ከዚህ ቀደም ጌታ ራሱ ይህንኑ ጥያቄ ተጠይቆ ደጋግሞእንደመለሰው[2] “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ ።” በማለት መለሰ። ጌታም የመልሱን ትክክለኝነት ለመመስከር ጊዜ አልወሰደበትም። ይህየአጽንኦት ምላሽ ግን አንድ ሃሳብ በውስጣችን መጫሩ አይቀርም። ያም ሃሳብ በዘላለም ሕይወትና ባልንጀራን እንደ ራስበመውደድ መካከል ያለው ተዛምዶ ነው። “የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” የሚለው የሕግ አዋቂው ጥያቄየዘላለም ሕይወት ሕግን በመፈጸም የሚገኝ መሆኑን የሚጠቁም ቢሆንም የጌታ መልስና የታሪኩ ድምዳሜ ግን የሕግንፊደል በመፈጸም እንደማይገኝ ያረጋግጣል። ምክንያቱም ከልጅነቱ አንስቶ ሕግን ፈጽሜያለው እያለ የሚመጻደቀውን ሰውየአንድን ሳምራዊ ታሪክ ጠቅሶ “ሂድ፥ አንተም እንዲሁ አድርግ” ሲለው “እስካሁን አላደረክም!” እያለው እንደ ሆነ ግልጽ ነው። የዘላለም ሕይወት የሕግ ፍጻሜ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን እንጂ በሕግ ሥራ አይገኝም። ነገር ግን በኢየሱስክርስቶስ በማመን የተገኘው የዘላለም ሕይወት፣ የሕይወቱ ሕግ በሆነው እግዚአብሔርን እና ባልንጀራን በመውደድ በተግባርይገለጣል። እግዚአብሔርንም ሆነ ባልንጀራን መውደድ በልብ ውስጥ ተቋጥሮ የሚቀር ስሜት ሳይሆን በድርጊት የሚገለጽተግባር ነው። ለዚህ ነው የዘላለም ሕይወት በማድረግ አይገኝም ነገር ግን በማድረግ ይገለጣል የምንለው። ማድረግ ትልቅሥፍራ እንዳለው የሚያሳየን በዚህ አጭር ክፍል ውስጥ ብቻ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ የተነሳው። “… ምን ላድርግ? (ቁ.25) … ይህን አድርግ! (ቁ.28)… ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ! (ቁ. 37)”። ስለዚህ እግዚአብሔርንም ሆነ ባልንጀራን መውደድ በሥራየሚገለጥ የሕይወት ባሕሪ እንጂ ስሜትና ቃል አይደለም።

ለዚህ ሕግ አዋቂ ፈተና የሆነበት የእነዚህ ሁለት ትዕዛዛት አለመነጣጠል ነው። እሱ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ፣ በፍጹምነፍስ፣ በፍጹም ሃሳብና በፍጹም ኃይል መውደድ ላይ ጥያቄ የለበትም። ጥያቄው ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ላይ ነው። ችግሩ እነዚህ ሁለቱ ትዕዛዛት ሁለት የተለያየ ክፍል ውስጥ ይጻፉ እንጂ (ዘዳ. 6፥5፤ ዘሌ. 19፥18) ፈጽሞ የማይነጣጠሉመሆናቸው ነው። እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስ፣ በፍጹም ሃሳብና በፍጹም ኃይል መውደድ በተግባር ሊገለጥየሚችለው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረውን በአጠገባችን ያለውን ሰው እንደ ራሳችን በመውደድ ብቻ ነው።

በቀጣይነት የዚህን ሰው የልብ ሁኔታ የሚገልጥልን “ባልንጀራዬስ ማነው?” የሚለው ሁለተኛው ጥያቄው ነው። ችግሩ ምንላይ ነው? እንል ይሆናል። ጸሐፊው አሁንም ከጥያቄው ባሻገር ጥያቄው የመነጨበትን የልብ ሁኔታ “ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ” በማለት ይገልጽልናል። የዘላለም ሕይወት ለመውረስ መንገዱ “… ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ነው!” በማለት የመለሰውሰውዬ አፍታም ሳይቆይ ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ “ባልንጀራዬስ ማነው?” ብሎ ሲጠይቅ መስማት የሚያስገርም ነው። ይህ ሰውየወደደው እግአብሔርን ወይም ባልንጀራውን ሳይሆን ራሱን ነው። “ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ …” ይለናላ! ስለዚህእግዚአብሔርንም ሆነ ባልንጀራን ለመውደድ ዋነኛው ዕንቅፋት ራስን መውደድ ነው። ራስን መውደድ ተፈጥሯዊ ስለሆነበራሱ ምንም ችግር የለበትም። ሰው ራሱን አለመውደድ አይችልም። ራሳችንን ለመውደድ እኛ የምንጨምረው ነገር የለም።ሰው ራሱን ለመውደድ ትንሿን ጣቱን እንኳ ማንቀሳቀስ አይኖርበትም። በቃ! ሰው ሁሉ ራሱን የሚወድበት በቂ ነገር አለው።ራስን መውደድ ቁልቁለት ነው። ጥረት አይፈልግም፣ እንዲያውም ራሱ ያንደረድራል። ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ግንዳገት ነው። ጥረት ይጠይቃል። ያም ጥረት ያለ ክርስቶስ ሕይወትና ያለ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት ሊሳካ አይችልም። ለዚህ ነውመለኮታዊ ትዕዛዝ ሆኖ የመጣው። የእግዚአብሔር ፈቃድ ትኩረታችን ከራሳችን ተነስቶ ሌላው ሰው ላይ እንዲሆን ነው።ትኩረቱ ራሱ ላይ የሆነ ሰው እግዚአብሔርንም ሆነ ሌላውን ሰው ሊወድ አይችልም።

በምሳሌው ላይ የምናያቸው ካህን እና ሌዋዊ በወንበዴዎች እጅ የወደቀውን ሰው አይተው ገለል ብለው ያለፉት ራሳቸውንስለወደዱ ነው። በሞትና በሕይወት መካከል ሆኖ የወደቀውን ሰው ሲያዩ ፈጥኖ የመጣላቸው ዘኁልቁ 19፥11 ላይ የሚገኘው“የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል።” የሚለው ቃል ነው። ይህ ሕግ የተሰጠው የእስራኤልን ሕዝብከበሽታና ከወረርሽኝ ለመጠበቅ ነው። ሕግ ሥጋና መንፈስ አለው። መላውን ሕግ በሰው መስለን ብንመለከት ሥጋውየሚታየው ውጪያዊው ማንነቱ ሲሆን መንፈስ የማይታየው ውስጣዊ ማንነቱ ነው። ሥጋው ፊት ለፊት የሚታይ ቢሆንምበሕይወት የሚያኖረውና የሚያንቀሳቅሰው በውስጥ ያለው የማይታየው መንፈሱ ነው። ሥጋ ከመንፈስ ሲለይ ይሞታል፣ይበሰብሳል። በሙሴ መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን ሕግጋት እንደ አካል፣ እያንዳንዱንም ነጠላ ሕግ እንደ ብልት ወይም የአካልክፍል ብንመለከታቸው ጥሩ ስዕል ይሰጥናል። ዘዳ. 6፥5 እና ዘሌ. 19፥18 የሕጉ መንፈስ ናቸው። ስለዚህ በድፍረት ፍቅር የሕጉመንፈስ ነው ማለት እንችላለን። ፍቅር ደግሞ ራስን ሳይሆን ሌላውን ስለ መውደድ ነው። ስለዚህ በድን አትንካ የሚለውሕግ አንድ ሰው የተጎዳን ሰው እንዳይረዳ ለመገደብ ታስቦ ሳይሆን ሲነካ ሳይታወቀው በእጁ ወይም በልብሱ በሽታ አምጪባክቴሪያዎችንና ጀርሞችን ስለሚሸከምና ሄዶ ሌላውን ሰው ሲነካ በሽታ ስለሚያስተላልፍ ወረርሽኝን ለመከላከል ታስቦ የወጣከራስ ይልቅ ባልንጀራን የሚጠብቅ የፍቅር ሕግ ነው። ነገር ግን በዘኁልቁ 19 ላይ እንደምናነበው እግዚአብሔር ለዚህ ችግርአስቀድሞ መፍትሄ ሰትቷል። ከሰፈር ውጪ ከሄሶጵ እና ከወይራ እንጨት ጋር የተቃጠለ የቀይ ጊደር አመድ ኬሚካሊ አልካላይንስለሆነ ጀርሞቹንና ባክቴሪያዎቹን ይገድላቸዋል። ስለዚህ በድን የነካው ሰው ለሰባት ቀን ራሱን ያግልል፣ በሦስተኛውናበሰባተኛው ቀን በዚህ ውሃ ይታጠብ ከዚያ ይነጻል ይለናል።

ካህኑና ሌዋዊው ራሳቸውን ስለወደዱ፣ ራሳቸውን ማጽደቅ ስለፈለጉ፣ ለአንድ ሳምንት ወይም ለሰባት ቀናት ራሳቸውንለማግለልና የመንጻት ሥርዓት ለመፈጸም ስላልፈለጉ የወደቀውን ሰው ገለል ብለው አለፉት። ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ሕጉንከመጠን በላይ ለጥጠው፣ አትንካ የሚለውን አትቅረብ ስትቀርብ ጥላህ ካረፈበት ያረክሳል ስለሚሉ ካህኑም ሆነ ሌዋዊውበሕይወት መኖር አለመኖሩን ቀርበው ለማጣራት አልሞከሩም። ሰውየው ግን ከድብደባው የተነሳ ራሱን ሳተ እንጂ በሕይወትነበር። የሕጉን አንድ ክፍል ለመፈጸም ሲተጉ የሕጉን መንፈስ ሻሩት። ሕግን ለመጠበቅ ሲባል ሕግን መሻር ይሏል ይህ ነው።ነገር ግን ያ ሕግን አያውቅም፣ በዘርም በእምነትም ዲቃላ ነው የሚሉት ሳምራዊ የወደቀውን ሰው አይቶ አዘነለት ቀርቦምረዳው እንጂ ለራሱ አላሰበም። በዚህም ባልንጀራውን እንደ ራሱ በመውደድ ሕግን ሁሉ ፈጸመ። መጽሐፍ እንዲህይላልና፦ “ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው።” ገላ. 5፥14

“እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። አታመንዝር፥ አትግደል፥አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድበሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።” ሮሜ 13፥8-10

ሳምራዊው የወደቀውን ሰው አይቶ አዘነለት። ራሱን ከወደቀው ሰው ጋር አዛመደ። ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ በሃሳብምሆነ በስሜት ራስን ከተጎዱ ሰዎች ጋር ከማዛመድ ይጀምራል። ሆኖም በዚያ አላበቃም፤ ዋጋ ከፈለ። ባልንጀራን እንደ ራስመውደድ በሃሳብና በስሜት ራስን ከማዛመድ ባሻገር መስዕዋትነት በመክፈል፣ በመቆረስ ይገለጣል። ሳምራዊው የተጎዳውንሰው ለማዳን ዘይቱን አፈሰሰ፣ የወይን ጠጁን አፈሰሰ፣ ጨርቁን ቀደደ፣ እሱ በእግሩ እየሄደ ራሱን የሳተውን ሰው በእንሰሳውላይ ጫነ፣ ገንዘቡን ከፈለ፣ ጊዜውን አቃጠለ፣ ዕንቅልፉን አጣ፣ ካሰበው ከእቅዱ ወጣ። እገዛው ቅጽበታዊ ወይም ቁንጽልአልነበረም። እንግዶች ማረፊያ ወስዶ እስኪነቃ ጠበቀው፣ ፈጽሞ እስኪድን እንዲጠብቀው ለአሳዳሪው ዐደራ ሰጠው። ከዚህ በላይ ምን መስዋዕትነት አለ? ሁኔታው የጠየቀውን ሁሉ ከፈለ። በዚህ ሰው ውስጥ የዘላለም ሕይወት የሆነውንየክርስቶስን ባሕሪ ተንጸባርቋል። የእግዚአብሔር የጽድቅ ሕግ የሚጠይቀው ሁሉ ተፈጽሟል ።

ሕግ አዋቂው ግን “የቀረኝ ባልንጀራ ማነው? በአጠገቤ ያሉትን ባልንጀሮቼን ሁሉ እወዳለሁ።” በማለት የራሱን ጽድቅሊያቆም ሲታገል ለእግዚአብሔር ጽድቅ መገዛት አልቻለም። እሱ ባልንጀሮቼ የሚላቸው በፈሪሳውያን ወገን ውስጥ ያሉትን“ኼቨሪም” ወይም ጓዶች እንጂ ሌሎችን አልነበረም። ነገር ግን አንድ ያልገባው ትልቅ እውነት ነበር። ልብ ብሎ ቢያነበው በገዛአንደበቱ የጠቀሰው “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ጥቅስ የሚገኝበት የዘሌዋውያን 19 ዐውድ ባልንጀራው ማንእንደ ሆነ ይነግረው ነበር። ዘሌዋውያን 19፥18 “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ከማለቱ በፊት በቁጥር 10 ላይ ስለ ድሆች፣ስለ መጻተኞችና ስደተኞች፤ በቁጥር 13 ላይ ስለ ቀን ሠራተኞች ወይም ለፍቶ አዳሪዎች፤ በቁጥር 14 ላይ ቋሚ የአካል ጉድለትስላለባቸው ሰለ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፣ በቁጥር 15 ላይ ስለ ወደ ፍርድ ቤት ስለሚጎተቱ ድሆች ያወሳል። ስለ እነዚህ ጋርከነገረን በኋላ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ካለን ባልንጀሮችህ እነዚህ ናቸው እያለን ነው። ስለዚህ ባልንጀራዬ ማነውለሚለው የመመጻደቅ ጥያቄ መልሱ በአጠገብህ ያለ የአንተን ዕርዳታ የሚሻ ወይም የምትሻ ማንኛውም ሰው የሚል ነው።እንደ ራሳችን እንድንወዳቸው የታዘዝናቸው ባልንጀሮቻችን በዙሪያችን ያሉ ድሃ አደጎች፣ አካለ ጎዶሎዎች፣ ተፈናቃዮች፣ስደተኞች፣ ጎስቋሎችና ምስኪኖች ናቸው።

ውድ ወገኖቼ በጌታ በኢየሱስ በማመን የዘላለም ሕይወት አግኝታችኋል? የዘላለም ሕይወት ከሞት ባሻገር የሚገኝ፣ ከዕለታትአንድ ቀን የሚመጣ፣ ያለማቋረጥ የሚኖርበት ዘመን ሳይሆን ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በሥጋ የተገለጠ ኅልው አካል ነው።ስሙም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል። በእርሱ ያመነ ሕይወት አለው። ይህ ሕይወት በደፈናው “በውስጤ አለ” የምንለው ብቻሳይሆን መኖሩ በፍሬ የሚገለጥ ነው። የሚገለጠውም በዙሪያችን ላሉ፣ በመንገዳችን ለምናገኛቸው ድሃ አደጎች፣ አካለጎዶሎዎች፣ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች፣ ጎስቋሎችና ምስኪኖች በምናሳየው ርህራሄና መስዋዕትነት ነው። የእንትን ቤተክርስቲያንአባል ነኝ፣ በዚህ በዚህ ዘርፍ አገለግላለሁ፣ አሥራቴን እሰጣለሁ፣ ከጓደኞቼ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ … ወ.ዘ.ተ በሚልራሳችንን ልናጸድቅ አይገባም። ይልቅ እንነሳና በዙሪያችን ያሉትን በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩት ወገኖች እንታደግ።ሕይወታቸውንም በዘላቂነት ለመለወጥ እንስራ።

[1] ሉቃስ 20፥27፤ ማቴ. 22፥23፤ ማር. 12፥18-27፤ ሐዋ. ሥራ 23፥8 | [2] ማቴ. 22፥37-39፤ ማር. 22፥28-31