Love your Neighbor

ከፊታችን ያለውን ሰፊ የሥራ መስክ ከግምት በማስገባት ከአጋሮቻችን ጋር የላቀ የግንኙነት መስመር መገንባት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው ከያዝነው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት (2016 ዓ.ም) በመነሳት በየወሩ የሥራችንን ሂደትና የጊዜውን ቃል ወደ እርስዎ የሚያደርስ አጭር ዘገባ ለመሥራት ወስነናል። ከዚህም በመነሳት ይህ አሁን እያነበቡት ያሉት የጥቅምት (ኦክቶበር) ወር 2016 ዓ. ም የጊዜው-ቃል መልዕክት ሲሆን መሰል ዘገባዎች ወር በገባ የመጀመሪያ እሁድ ያለማሰለስ ወደ እርስዎ እንዲደርሱ እንጥራለን። 

የዛሬ እንግዳ፣ የነገ ወራሽ

ቀዳሚ ሰማዕት የሆነው እስጢፋኖስ በእስራኤል ሸንጎ ፊት ተከሶ ቀርቦ መልስ ሲሰጥ ያቀረበውን ሰፊ ትረካ የጀመረው የክብር አምላክ ለአባታችን አብርሃም ገና በካራን ሳይቀመጥ በከለዳዊያን ዑር ሳለ ታይቶ ወደ ከነዓን ምድር እንዳመጣው በመተረክ ይጀመራል። እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውም የተስፋ ቃል “ይህችን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ።” የሚል ነበር። ይህንኑ ተመሳሳይ ተስፋ አብርሃም ከሞተ በኋላ ለይስሐቅ ከዚያም ለያዕቆብ ደግሞታል። ከዚህም በመነሳት ተስፋው ምድርን የመውረስ ተስፋ መሆኑን በግልጽ እናያለን።

ሆኖም እነዚህ የእምነት አባቶች ሊወርሱት በወጡት ምድር ላይ የኖሩትን ኑሮ ስንመለከትና ስለ ራሳቸው ይሰጡት የነበረውን ምስክርነት ስንሰማ ከተሰጣቸው ተስፋ ጋር ተጻራሪ የሚመስል እውነታ እናያለን። ይህንንም የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊ በአስራ አንደኛው ምዕራፍ ላይ እንዲህ በማለት በግልጽ አስፍሮልናል፦

“ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና። … እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ።እንዲህ የሚሉት ለእነርሱ የሚሆነውን አገር እንዲፈልጉ ያመለክታሉና። ያን የወጡበትን አገር አስበው ቢሆኑ፥ ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር፤ አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።”  ዕብ. 11፥8-16

ጥያቄው እነዚህ ለመውረስ የተጠሩና ጽኑ ተስፋ የተቀበሉ የእምነት አባቶች በኖሩበት ዘመን “ወራሽ ነኝ!” ሳይሆን “እንግዳ ነኝ!” ለምን አሉ? የሚለው ነው።

ለካ እግዚአብሔር አብርሃምን ከአገሩና ከዘመዶቹ፣ ከአባቱም ቤት ለይቶ ሲያወጣውና ሊያወርሰው ወዳለው ምድር ሲያመጣው እርሱም ሆነ ዘሩ በቀጥታ እንዲወርሱት ሳይሆን በአሁኑ ዘመን በእንግድነት ኖረውና በምድር ላይ ፈቃዱን አድርገው እንዲሞቱና በጌታ ቀን መለከት ሲነፋ ከሙታን ተነስተው እንዲወርሱ ነው። ኃጢአተኞች በሚሰለጥኑበት፣ የወደቁት መላዕክት ምድርን በሚገዙበት፣ ኃጢአት እንደ ውሃ በሚጠጣበት፣ ጣዖት አምልኮ በነገሠበት ዘመን ያለ እግዚአብሔር ሊወርሱና ሊነግሡ አልወደዱም። ነገር ግን ከተገለጠላቸው ክብር ጋር ተጻራሪ በሆነ ዓለም ውስጥ እንግዶችና መጻተኞች እንደ ሆኑ ታምነው በመኖርና አምነው በመሞት እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ከሙታን አስነስቶ ክብሩ ያለበትን፣ ጽድቁ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደሚያወርሳቸው ታመኑ። ነገ የእነርሱ እንደ ሆነ በማመን ዛሬን በእንግድነት ኖሩ። በዕለት ተዕለት ኑሯቸው በዘመኑ የአመጽ መረብ ሳይጠላለፉ ተዘልለው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እያደረጉ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መዝገብ ሰበሰቡ።

ዛሬ እኛ የእምነት ልጆቻቸው የምስክር ደመናዎቻችን የሆኑትን፣ ወደ ከበረ ተስፋችን በምናደርገው የእምነት ጉዞ እንደ ደመና ዐምድ በዙሪያችን ሆነው አቅጣጫ የሚጠቁሙንን የእነዚህን የእምነት አባቶች ምሳሌ ተከትለን በዚህ ጠማማና አመጸኛ ትውልድ መሀል በእንግድነት መንፈስ ልንኖርና ከግርግሩ ወጥተን በሚመጣው ዘመን የምንከብርበትን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እያደረግን ለሚጠይቁን ሁሉ “የዛሬ እንግዳ፣ የነገ ወራሽ ነኝ!” እያልን ልንኖር ይገባናል።

ዛሬ ላደርገው የሚገባኝ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምንድነው? ለሚል ሰው በቅዱስ ቃሉ ፍንትው ብሎ የተቀመጠ፣ መንፈስ ቅዱስም በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ጆሮ ላለው ሁሉ የሚያሰማው መልዕክት ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን በመውደድ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩትን እንድንረዳና የተስፋውን ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ እንድናውጅ ነው። ይህንንም ስንችል በግንባር፣ ካልሆነም በጉልበት (በጸሎት)፣ ደግሞም በገንዘብ ልናደርገው ይገባናል።

ያሬድ ጥላሁን (ወንጌላዊ)

ጥቅምት 2016 ዓ. ም

2 Comments

  • Asher Milkyas Boerna says:

    Great

  • Jabez says:

    “ዛሬ እኛ የእምነት ልጆቻቸው የምስክር ደመናዎቻችን የሆኑትን፣ ወደ ከበረ ተስፋችን በምናደርገው የእምነት ጉዞ እንደ ደመና ዐምድ በዙሪያችን ሆነው አቅጣጫ የሚጠቁሙንን የእነዚህን የእምነት አባቶች ምሳሌ ተከትለን በዚህ ጠማማና አመጸኛ ትውልድ መሀል በእንግድነት መንፈስ ልንኖርና ከግርግሩ ወጥተን በሚመጣው ዘመን የምንከብርበትን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እያደረግን ለሚጠይቁን ሁሉ “የዛሬ እንግዳ፣ የነገ ወራሽ ነኝ!” እያልን ልንኖር ይገባናል”

    ለእኔ ትውልድ ፤ የትም ፍጪው ዱቄቱንም አምጪው በሞላበት ትውልድ ይህን የመሰለ መልዕክት ማስተላለፍ ትልቅ ማስተዋል መስማት ደግሞ ትልቅ በረከት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *