Love your Neighbor

“… የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።” ያዕ. 5፥16

የዚህ መልዕክት ጸሐፊ “የጌታ ወንድም” በመባል የሚጠራው ያዕቆብ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በነበረችው የመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን በስፋት የሚታወቀው በሁለት ዐበይት ነገሮች ነበር። የቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚያስተምረን ያዕቆብ የሚጠራበት ቅጽል ስም “ጻድቅ” የሚል ሲሆን የሚነገርለት ልዩ ማንነቱ የጸሎት ሰውነቱ ነበር። ከላይ በተጠቀሰው ክፍል ሁለቱም ማንነቶች በአንድነት ተቀምጠዋል፤ ጽድቅ እና ጸሎት።

 

ለያዕቆብ ጽድቅ ሰው በጥረቱ የሚያመጣው ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚገኝና እግዚአብሔር በቃሉ አማካይነት በእምነት ለሰው የሚያካፍለው ችሮታ ነው። “የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።”1፥20 ሲል ጽድቅ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚገኝ እንጂ ሰው ለእግዚአብሄር በመቅናትና በመጣላት የሚያመጣው እንዳልሆነ እየነገረን ነው። ይልቅ ጽድቅ እምነት አክባሪው እግዚአብሔር በማጽደቅ ችሎታው ለሚታመን ሰው እምነቱን በጽድቅ እንደሚለውጥለት ማለትም እምነቱን ጽድቅ አድርጎ እንደሚቆጥርለት የእምነት አባት የሆነውን አብርሃምን ጠቅሶ ይጽፍልናል። “መጽሐፍም፦ አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ …” 2፥23። ይህም ጽድቅ ከዓለም ምኞት ራስን በመጠበቅ፣ በእያንዳንዱ ሁኔታ በእግዚአብሄር በሙሉ ልብ በመታመንና ለሰዎች መልካም በመሥራት የሚገለጽ እንደ ሆነ ይጽፍልናል። ከሰማይ የመጣው የእግዚአብሔር ጽድቅ ባመኑትና በተቀበሉት ብሎም በሚተገብሩት ሰዎች አማካይነት በምድር ላይ ይዘራና በዝቶና ተትረፍርፎ የፍሬ መኸር ይሆናል። ታዲያ ጽድቅ የሚዘራው በሰላም እርሻ ላይ ነው። ከእግዚአብሔር እና ከሰዎች ጋር ሰላም ከሌለን ጽድቅ ይጠወልጋል፣ ፍሬውም ይረግፋል፣ ድርቅና ረሃብ ይወርሰዋል። ሰው ሁለት ወዳጅ አለው፤ እግዚአብሔርና ሰው። ከሁለቱም ጋር የሚያጣላው አንድ ነገር ቢኖር የዓለምና የሥጋ ምኞት ነው። ምኞት የማትታይ ጽንስ ብትሆንም ከተንከባከብናትና ካሳደግናት ኃጢአትንና ሞትን ወልዳ ከሁለቱ ሰብዓዊና መለኮታዊ ወዳጆቻችን ትለየናለች።

 

በምኞት ከሰውና ከእግዚአብሄር ጋር የተጣላ አማኝ የፈለገውን ያህል ረዥም ጸሎት ቢጸልይ፣ የፈለገውን ያህል ቢጮህና ቢወራጭ ጸሎቱ ፍሬ ከርስኪ ነው። በእግዚአብሔር ታምኖ፣ ሰውን አፍቅሮ መልካም እያደረገና ጽድቅን በሰላም እርሻ ላይ እየዘራ የሚኖር ሰው ጥቂት ጸሎቱ ታላቅ ኃይል ያደርጋል። ውሱን ሰው ሆኖ ወሰንየለሽ ተግባር ይከውናል። የእግዚአብሄርን ክንድ ያንቀሳቅሳል። ዝናብን በወቅቱ ማዝነብ የመለኮት ሥራ ነው። ሰው የሆነው ኤልያስ ግን እንዳይዘንብ ሰማዩን ዘጋ፣ ደግሞም ከፈተ። ነቢዩ ኤሊያስ በቀርሜሊዮስ ተራራ የእስራኤልን ሕዝብ ሰብስቦ ከአራት መቶ ሃምሳ የባኦል ነቢያትና ጋር በተፋጠጠበት ጊዜ የጸለየው ጸሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡ ጸሎቶች ሁሉ አጭሩ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

 

“አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ። አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ አለ።”1 ነገሥ. 18፥36-37

 

ከዚህ ክፍል የምንማረው እውነት የሚሰማና ኃይል ያለው የሚሠራም ጸሎት ከምንደረድረው ቃላትና ከምናሰማው ጩኸት ይልቅ የኑሯችን ውጤት መሆኑን ነው። እግዚአብሔር ጸሎትን ሲሰማ “ምን አልክ? ወይም ምን አልሽ?” ብሎ ሳይሆን “ማን ነህ? ወይም ማን ነሽ?” ብሎ ነው። ስለዚህ ኑሯችንን እንመርምር። እግዚአብሔር ብቸኛ መታመኛዬ ነው! እንበል። ሰዎችን ሁሉ እንውደድ፣ የእኛን ድጋፍና ዕርዳታ ለሚፈልጉ ሁሉ እንዘርጋ። ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንውደድ። ሰዎችን በሃብታቸውና በውጪያዊ ገጽታቸው ሳይሆን በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ በመፈጠራቸው እናክብራቸው። ከዚህ ጎድለን ከተገኘን በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን አዋርደን ንስሐ እንግባ። በግል ለበደልናቸውም ኃጢአታችንን እንናዘዝ። ያኔ ፈውሳችን ይበቅላል፣ ተሐድሷችን ይፈጥናል። ጸሎታችንም ተሰምቶ ታላቅ የኃይል ሥራ ይሠራል።