Love your Neighbor

አንድ ሰው

 

“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ …” ሉቃስ 10፥30

 

ምን ዓይነት ሰው? ነጭ ወይስ ጥቁር? ሀብታም ወይስ ድሃ? ክርስቲያን ወይስ እስላም? አማራ ወይስ ኦሮሞ? መጤ ወይስ ተወላጅ? ምሁር ወይስ ገበሬ? ይህ ሁሉ ምን ያስፈልጋል? በቃ! አንድ ሰው። ሰው የሆነ ሰው። ቅጽሉ ወይም መገለጫው ሰውየውን ሰው አላደረገውም። ሰው ለመሆነ የግድ ነጭነትን ወይም ጥቁርነትን ማሟላት አይጠይቅም። ሀብታም ስለሆነ ሰው፣ ድሃ ሰለሆነ ደግሞ ሌላ ነገር አይሆንም። ዘሩ፣ ሙያው፣ የትምህርት ደረጃው ወይም ሌላ ሁሉ መገለጫዎቹ እንጂ ማንነቱ አይደሉም። አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ብዙ መገለጫዎች ሊኖሩት ይችላሉ። አንዳንዶቹ ጊዚያዊ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ዘላቂ ይሆናሉ።

 

ለምሳሌ ዛሬ ተማሪ የሆነና በዚህ ማንነቱ ያወቅነው ሰው ሲመረቅ ምሩቅ፣ ሲቀጠር ሠራተኛ፣ ጡረታ ሲወጣ ጡረተኛ ይባልና መታወቂያዊን ይቀይራል። ዛሬ የዚህ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው ነገ መረዳቱ ይለውጥና በሌላ መገለጫ ይከሰታል። ዛሬ በድህነት የፈረጅነው ሰው ነገ በለስ ቀንቶት ቱጃር ይሆንና አጠራራችንን ለመቀየር እንገደዳለን። በቀላሉ የሚቀየሩ የማይመስሉን እንደ ቆዳ ቀለምና እንደ ብሔር ያሉ ልዩነቶችም ቢሆኑ ውጪያዊና ገጻዊ ናቸው። ዛሬ ነጭ፣ ጥቁር፣ ቢጫ … ያልነውን ነገር በአንድ መጠሪያ አስከሬን ከዚያም አፈር … እንለዋለን። ሰው የቆዳ ቀለሙ ቢለያይም ደሙ አንድ ነው፤ እንጂ የአንዱ ደም ሰማያዊ የሌላ ግራጫ ሊሆን አይችልም። የሰው ሁሉ ደም ቀይ ነው። ሰው ከአንድ ተፈጥሯልና በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት ሰው የለም!

 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕግ አዋቂው ለቀረበለት “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” የሚለው ጥያቄ አጭር ቀጭን መልስ ከመስጠት ይልቅ ወግ አዋቅሮ፣ ኹነትና ሴራ ቀምሮ፣ ገጸ-ባሕሪያት ሰድሮ በእውነታ የታጀበ ምሳሌያዊ ታሪክ መተረክ መርጧል። ሆኖም ባጠቃላይ ክፍሉ ውስጥ የተጠቀሱት ገጸ-ባሕሪያት ሁሉ ውጪያዊ መገለጫ ቢኖራቸውም ከታሪኩ መነሻ እስከ መጨረሻ የሚታየውን መሪ ገጸ ባሕሪ ውጪያዊ ማንነት አላላበሰውም። ይህም ሆን ብሎ እንደ ተደረገ መገመት አያስቸግርም። ሰው በውጪያዊ ማንነቱ በሚመዘንበት በያኔው ዓለም ከሰውነቱ ውጪ ምንም ዓይነት ሌላ መገለጫ የሌለው ገጸ-ባሕሪ መሳል ታስቦበት ካልሆነ ባጋጣሚ የሚመጣ አይደለም። በክፍሉ ውስጥ ጠያቂው የተገለጠው “ሕግ አዋቂ” በሚል ስያሜ ነው።  

 

በምሳሌውም ውስጥ የታሪኩ ማጠንጠኛ ከሆነውና በወንበዴዎች እጅ ከወደቀው ሰው በቀር ሁሉም ውጪያዊ መገለጫ አላቸው። ወንበዴዎች፣ ካህን፣ ሌዋዊ እና ሳምራዊ ሰው። በወንበዴዎች እጅ የወደቀው ግን “አንድ ሰው” ከሚል በቀር ሌላ መገለጫ አልተሰጠውም። ይህም “ባልንጀራዬ ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “በመንገድህ የሚገጥምህ፣ የአንተን ዕርዳታ የሚሻ ማንኛውም ሰው!” የሚል መሆኑን ያስገነዝበናል።

 

ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ የሚወስደው መንገድ በተፈጥሮው አስቸጋሪ፣ ወንበዴዎች ዘርፈው ለመሰወር የሚያመቻቸው በመሆኑ በርካታ ጥቃቶች ደጋግመው ይከሰቱ እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ከዚህም የተነሳ “የደም መንገድ” የሚል መጠሪያ እንዲሰጠው አድርጓል።

 

ስለ መንገዱ መልክዓ ምድራዊ ገጽታ ጥሩ ስዕል የሚሰጠን የቤተክርስቲያን መጋቢና የነጻነት ተሟጋቹ የነበረው ዶ/ር ማርቲን ሉተግ ኪንጅ ጁኒየር በግፍ ከመገደሉ አንድ ቀን በፊት በመንፌስ ቴነሲ በሚገኘው በርካታ አፍሪካዊ-አሜሪካውያን በሚሰበሰቡበት የማሶን መቅደስ ባደረገው “ከተራራው ጫፍ ላይ ደርሻለሁ” በተሰኘው ታሪካዊ ንግግሩ ውስጥ የጠቀሰው ሃሳብ ነው።[1] በንግግሩ መሀል ዶ/ር ኪንግ

 

ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ስለሚወስደው መንገድ ለባለቤቱ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እኔና ወይዘሮ ኪንግ መጀመሪያ ኢየሩሳሌም የነበርንበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። መኪና ተከራይተን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሄድን። በዚያ መንገድ እየነዳን ሳለ ባለቤቴን፣ “ኢየሱስ ይህንን ስፍራ ለምን የምሳሌው መቼት አድርጎ እንደተጠቀመበት አሁን ገባኝ” አልኳት። ጠመዝማዛና ውጣ ውረድ የበዛው መንገድ ነው። በእውነትም ለወንበዴዎች ምቹ ነው። ጉዞ ከኢየሩሳሌም ከባህር ጠለል በላይ በ1200 ጫማ ከፍታ ይጀመርና ከአስራ አምስት ወይም ከሃያ ደቂቃ ጉዞ በኋላ ወደ ኢያሪኮ ሲወረድ ከባህር ጠለል በታች 2200 ጫማ ጥልቀት ላይ ይደረሳል። ይሄ እውነትም አደገኛ መንገድ ነው።”1

 

ይህ ሰው መንገደኛ ነው። በወንበዴዎች እጅ ለመውደቅ አላቀደም። ወንበዴዎቹም ይህ ሰው በዚያ መንገድ እንደሚያልፍ መረጃ ደርሷቸው አልጠበቁትም። የገጠማቸው ሌላም ሰው ቢሆን እንደማይምሩት የታወቀ ነው። ወንበዴዎች ናቸዋ! ዓላማቸው መዝረፍና መሰወር ነው። በዘመኑ ልብስ ውድ ሃብት ነው። ባለጠጎች ንብረት ሲያከማቹ ከወርቅና ብር ቀጥሎ የሚያስቀምጡት አንዱ ልብስ ነው።2 መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ንስሐ ሲሰብክ “ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል” ሉቃስ 3፥11 ሲል ሁለት ልብስ መኖር እንደ ቅንጦት፣ አንድ ልብስ እንደ በቂ ይወሰድ እንደ ነበርና አንዳች ልብስ የሌላቸውም እንደ ነበሩም ያሳየናል። በጊዜው ልብስ በእጅ ስለሚሠራ፣ ውድ ጥሬ ዕቃ ስለሚጠይቅ እና ረዥም ጊዜ ስለሚፈጅ እጅ ላይ እንዳለ ጥሬ ገንዘብ ይቆጠር ነበር። ዘራፊዎቹ ያለ ብዙ ትግል ልብሱን ለመግፈፍ ራሱን እንዲስትላቸው አስቀድመው ይመቱታል። ይህ ሰው ከድብደባው የተነሳ ክፉኛ እንደ ቆሰለና ራሱን እንደ ሳተ እናነባለን። በሕይወትና በሞት መካከል ያለ ሰው የሁለት አገር ተጓዥ ነው። ወይ ወደ ሕይወት ወይ ወደ ሞት፤ የቀረበ ይወስደዋል። ወደ ሕይወት የመመለሱ ነገር በዋነኝነት የሚንጠለጠለው ፈጣን ዕርዳታ በማግኘቱ ላይ ነው። ይህ ሰው የሚያስፈልገው ሰው የመሆን ዋጋ የገባውና እንደ ራሱ የሚያየው ሌላ ሰው ነው።

 

[1] Martin Luther King Jr., “I’ve Been to the Mountaintop” (April 3, 1968)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *