Love your Neighbor

የምሥጋና መንፈስ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ቆይታዬ ካደረኳቸው ቃለ-መጠይቆች መካከል “በልሳን መናገር” በሚል ርዕስ በኒቆዲሞስ ሾው ላይ ከጋዜጠኛ ትዕግስት እጅጉ ጋር ያደረኩት አንዱ ነው። ከሕዝብ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰበሰቡት ጥያቄዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ተጨምቀው ሲቀርቡልኝና ስመልስ በአዲስ ኪዳን ገጾች ላይ አንድ ሥርዓተ-ጥለት (ፓተርን) አስተዋልሁ። ከዚህ ቀደም ፈጽሞ ያላየሁት አዲስ ነገር ባይሆንም እንዲህ ነጠብጣቡን ገጣጥሜ አይቼው ግን አላውቅም ነበር። ዛሬ ስለ ልሳን መናገር የምናውቃቸውን እውነቶች የጻፉልን ሁለት የአዲስ ኪዳን ግዙፋን ወንጌላዊው ሉቃስና ሐዋርያው ጳውሎስ ናቸው፤ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ፣ ጳውሎስ በአንደኛ ቆሮንቶስ። ሉቃስ በልሳን መናገርን የሚያስቀምጠው ተናጋሪው ባልተማረው፣ ከዚህ ቀደም ተናግሮት በማያውቅ ነገር ግን ለሌሎች ቋንቋውን በሥርዓት ለሚያውቁ ሰዎች መልዕክት የሚያስተላልፉበት መንገድ እንደ ሆነ ነው። ጳውሎስ ግን በተለይ በአንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ አሥራ አራት ላይ ተናጋሪው የማይረዳው ብቻ ሳይሆን ካልተተረጎመ በስተቀር ማንም ሰው ሊያስተውለው የማይችል ነገር ግን በመንፈስ ወደ እግዚአብሔር የሚቃትትበት መንገድ እንደ ሆነ ይነግረናል። ሁለቱንም የሚያስተሳስራቸው አንድ ነገር ሲሆን እሱም የልሳኖቹ ያዘት ምስጋና ላይ ማተኮሩ ነው። ይህን ሃሳብ በሚገባ ለመረዳት እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በጥልቀት መመልከት ይጠቅማል። 

“እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም። ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ …” (1ቆሮ.14፥16-18)

ሉቃስም በበዓለ ሃምሳ ቀን የሆነውን ሲተርክ እንዲህ ብሏል፦

“ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፦ እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን? … የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን። ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው፦ እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ።” (ሐዋ. 2፥6-12)

በቆርኖሊዮስ ቤትም የሆነው ከበዓለ ሃምሳው የተለየ አልነበረም፦

“ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና።” ሐዋ.10፥45-46

ከዚህ የምንማረው መንፈስ ቅዱስ በማናውቀው ቋንቋ እንድንናገር ሲሰጠን የምንለው ለእኛ ባይገባንም ሊነገር በማይችል ቃላት እግዚአብሔርን እየባረክን፣ እያመሰገንንና ታላቅ ሥራውን እየተናገርን እንደ ሆነ መረዳት እንችላለን።

እንግዲህ ሳናውቅ የምናደርገውን ይህን ምሥጋና አውቀን ምን ያህል ልናደርገው ይገባን ይሆን?! ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች፦

“ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።” (5፥17-18)

እንደሚል በእርግጥ ለእኛ በጎና ፍጹም ደስ የሚያሰኘውም የእግዚአብሔር ፈቃድ ምስጋና ነውና በዚህ የታንክስ ጊቪንግ ወቅት ብቻ ሳይሆን ዘወትር እያንዳንዱን ቀን አስበንበትና ሆን ብለን በምስጋና ልንጀምርና ልንፈጽም ይገባናል።

መልካም የምሥጋና በዓል

ያሬድ ጥላሁን (ወንጌላዊ)

ጎልደን ኦይል አገልግሎት፣ ላቭ ዩር ኔበር

 

ባለ ራዕይ