Love your Neighbor

ብዙ ሰው አንድ መልክ

ስለ ሰው ስናስብ ፈጥኖ ወደ አእምሯችን ገዝፎ የሚመጣው ልዩነት ነው። የጾታ፣ የዘር፣ የቆዳ ቀለም፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የኑሮ ደረጃ፣ የኃይማኖት እና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች በዐይነ-ሕሊናችን ይደቀናሉ። በምድር ላይ የሰው ልጆች ቁጥር ከምንጊዜውም ይልቅ እየጨመረ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2023 ዓ.ምን ስንጀምር የዓለም ሕዝብ ቁጥር 7,942,645,086 እንደሚሆን ተገምቷል። ይህ ቁጥር 2022ን ስንቀበል ከነበረው በ 73,772,634 ጭማሪ አሳይቷል። ይህ ሁሉ ሕዝብ ራሱን ከሌላው የሚለይበት ዘርፈ-ብዙ አጥር አለው። አጥሩ እየጠበበና እየረዘመ እስከ ግለሰቡ ድረስ ይወርዳል። ይህም ዓለማችንን የልዩነት መናኸሪያ አድርጓታል። ሆኖም የሰው ልጅ ልዩነት ብቻ ሳይሆን አንድነትም እንዲኖረው ታስቦ የተፈጠረ ነው። አንድ ከሚያደርጉትም ነገሮች ዋነኛው የእግዚአብሔር መልክ ነው። የፍጥረታትን ሁሉ አጀማመር የሚተርክልን የዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ስለ ሰው አፈጣጠር ሲተርክ ትልቁን ስፍራ የሚሰጠው ለእግዚአብሄር መልክ ነው።

 

“እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።”ዘፍ. 1፥26-28

 

በዚህ ሥፍራና በሌሎች ግማሽ ደርዘን በሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ስለ መፈጠሩ የተጠቀሱትን ሃሳቦች በተመለከተ ምሁራን የተለያዩ አስተያየቶችን ይሰጣሉ። ከእነዚህም ውስጥ ጎልተው የሚታዩ ሦስቱ አመለካከቶች አሉ። አንደኛው መመሳሳል ላይ ያተኮረ ሆኖ ሰው በተፈጥሮው ከፈጣሪው ጋር የሚመሳሰል ማንነት እንዳለው የሚያስተምር ነው። ይህም መመሳሰል መንፈሳዊነትን፣ ምክንያታዊነትን፣ ፈቃዳዊነትን፣ ግንኙነታዊነትን እና ኢመዋቲነትን (የሰውን ነፍስ ሕያውነት) የተመለከቱ ባህሪያትን፣ ሥጦታዎችንና ጸባያትን ያዘለ እንደ ሆነ ያስተምራሉ።

 

ሁለተኛው አመከካከት ተዛምዷዊነት ላይ ተንተርሶ ሰው በሰማይም ሆነ በምድር ከተፈጠሩ ፍጥረታት በተለየ በተዛምዷዊ ባሕሪው ከፈጣሪው ጋር የሚመሳሰል ነው በሚለው ሃሳብ ላይ ይመሠረታል። ይህም አንዱ እግዚአብሔር በሦስት አካላት (ቅድስት ሥላሴ ወይም ልዩ ሦስትነት) ሕብረት ውስጥ ካለው ተዛምዶአዊ ግንኙነት ጋር የሚነጻጸር ነው።

 

ሦስተኛው አመለካከት ውክልና ላይ የሚያነጣጥር ሲሆን ሰው በፍጥረት የተካፈለው የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ሰው በማንነቱ ከሆነው ይልቅ በተግባሩ የሚገለጥ እንደ ሆነ ያትታል። ለምሳሌ ሰው ፍጥረታትን  ሲገዛ የሚያንጸባርቀው የእግዚአብሔርን የገዢነት ባሕሪ ነው። ይህም በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩን ያሳያል ይላሉ።

 

ለምሳሌ የሮም ቄሣር በሮም ቤተመንግሥቱ ተቀምጦ ያኔ በነበረው ዓለም በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እጅ ውስጥ መገኘቱ እንዲታወቅ በሮም ገንዘብ ላይ ምስሉን አስቀርጾ ነበር። ገንዘቡ ላይ ያለው የቄሣር መልክ በቀጥታ ቄሣርን አይደለም፤ ነገር ግን ይወክለዋል፣ ሥልጣኑን ያሳያል፣ ኃያል መገኘቱንም ያውጃል። ለዚህ ነበር ጌታ ኢየሱስ ለቄሣር ግብር ስለ መስጠት በተጠየቀበት ወቅት ገንዘቡን ተቀብሎ በላዩ ላይ የማን መልክ እንዳለ የጠየቀው። “የቄሣር” የሚል መልስ ሲሰጠው “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር አስረክቡ።” አለ (ማቴ. 22፥15) በእጅ በተሠራው ገንዘብ ላይ የቄሣር መልክ እንዳለ ከዚህም የተነሳ ለቄሣር ግብር እንደሚሠጠው ሁሉ በእናንተም ላይ በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር እጅ የተበጀ፣ በእስትንፋሱም የታተመ የእግዚአብሔር መልክ አለባችሁና ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ ማለቱ ነው።

 

መጽሐፍ ቅዱስ ከአዳም ዘር በተወለደ፣ በምድር ላይ በሚኖር ሰው ሁሉ ላይ የክብር ዘውድ የሆነው የእግዚአብሔር መልክ እንዳለ ይነግረናል። ሰውን ስንወድ የምንወደው የእግዚእብሔርን መልክ ነው። ሰውን ስንጠላ የምንጠላው የእግዚአብሔርን መልክ ነው። ሰውን ስንባርክ የምንባርከው የእግዚአብሔርን መልክ ነው፣ ሰውን ስንረግም የምንረግመው የእግዚአብሔርን መልክ ነው። (ያዕቆብ 3፥9-10) መልኩን ጠልቶ ሰውየውን መውደድ አይቻልም። መልኩን ረግሞ ሰውየውን መባረክ አይቻልም።

 

በአቅራቢያችን የምናያቸው፣ አይተንም እንዳላየ የምናልፋቸው በበርካታ የኑሮ ውጥንቅጥና ምስቅልቅል ውስጥ ያሉ የችግር መከራ የሚጠብሳቸው፣ የእጦት ጅራፍ የሚገርፋቸው ሰዎች እንወደዋለን፣ እናመልከዋለን፣ እናገለግለዋለን የምንለው የእግዚአብሔር መልክ ተሸካሚዎች ናቸው። በውድቀት ተገዝግዞ፣ በጨለማ ፈዞ አልታይ ብሎን ይሆናል እንጂ መልኩ አሁንም በላያቸው ላይ አለ። ብር ስለ ተጨማደደ፣ ሳንቲም ስለ ተቸረቸፈ ዋጋውን እንደማያጣ ሁሉ በእነዚህ ምስኪኖች ላይ በመለኮታዊ እጅ የተቀረጸው የእግዚአብሔር መልክ ዋጋው ትልቅና ዘላለማዊ ነው። ስለዚህ ልዩነቶችን ማቀንቀን ትተን አንድነታችንን እንዘምር። ልዩነቶቻችን ብዙና ውጪያዊ ናቸውና ሰባኪ አይፈልጉም፤ አንድነታችን ግን አንድና ውስጣዊ ስለሆነ አብዝቶ የሚያቀነቅነው ይሻል። ልዩነቶቻችን በሥጋ ዐይን በጉልህ የሚታዩ ናቸው። አንድነታችንን ለማየት ግን ብሩህ የልቦና ዐይን ይጠይቃል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን መልክ የምንወድ ከሆነ ድሆችን እንርዳ፣ ችግረኞችንና ምስኪኖችን እንደግፍ። የምናደርገውን ሁሉ ለባለ መልኩ እንደምናደርገው እንወቅ። ብድራታችንንም የሚከፍለን እሱ ነውና።